ሸማቹ በግልጽ ከተለጠፈ የዋጋ ተመን ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ለሚመለከተው አካል ማጋለጥ ይኖርበታል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ
ሸማቹ በግልጽ ከተለጠፈ የዋጋ ተመን ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ለሚመለከተው አካል ማጋለጥ ይኖርበታል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 17/2017 ሸማቹ ማኅበረሰብ በግብይት ወቅት በግልጽ ከተለጠፈ የዋጋ ተመን ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎች ሲያጋጥሙት ለሚመለከተው አካል በማሳወቅ መብቱን ማስከበር እንዳለበት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስገነዘበ።
በአዲሱ በጀት ዓመት ለንግዱ ማህበረሰብ የሚሰጡ አገልግሎቶችን የሚያሻሽሉና የሚያጠናክሩ አሰራሮች ተግባራዊ እንደሚደረጉም ተገልጿል።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ሀቢባ ሲራጅ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቢሮው በመዲናዋ የዋጋ ንረትን ለማስተካከልና ሸማቹን ማኅበረሰብን ተጠቃሚ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
ከዚህ መካከልም ከተማ አስተዳደሩ ባስገነባቸው የገበያ ማዕከላት፣ የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች ነጋዴው በቀጥታ ምርቶቹን ለሸማቹ እንዲያቀርብ ማድረግ አንዱና ዋነኛው መሆኑን አመልክተዋል።
በአቅርቦቱ ሸማቹን ተጠቃሚ ለማድረግ የተመቻቸ መሆኑን ጠቁመው፤ መንግስት ከሚያደርገው የቁጥጥርና ክትትል ስራ በተጨማሪም ማኅበረሰቡም ተሳታፊ በመሆን መብቱን ሊያስከብር እንደሚገባ ነው የገለጹት።
እያንዳንዱ የንግድ ተቋም የእቃዎችን ዋጋ ዝርዝር መለጠፍ እንደሚጠበቅበት ጠቁመው፤ ይህ ካልሆነ ግን ለሚመለከተው ማሳወቅ እንዳለበት ተናግረዋል።
በዋናነትም ሸማቹ በንግድ ቦታዎች በሚገበያይበት ወቅት ከተለጠፈ ዋጋ ውጭ የሚሸጡ ነጋዴዎችን ሲመለከት በ8588 ነፃ የስልክ መስመር በማሳወቅ መብቱን እንዲያስከብር ነው ቢሮ ኃላፊዋ ያሳሰቡት።
ቢሮው በአዲሱ በጀት አመት የንግድ ተቋማት አለ አግባብ እንዳይታሸጉና ነጋዴው ማኅበረሰብም ሕገ-ወጥ በሆኑ አካላት እንዳይጭበረበር ሚያደርጉ አሰራሮችን መዘርጋቱን ገልፀዋል።
በተለይ ለተቆጣጣሪ አካላት የደንብ ልብስ እንዲለብሱና የሚይዙት መታወቂያ ልዩ የመለያ ኮድ ወይም ባር ኮድ እንዲኖረው እየሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ቢሮ በአዲሱ በጀት ዓመት ነጋዴው ማህበረሰብ የንግድ ሕጉን ተከትሎ እንዲሰራ ለማድረግ የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለንግዱ ማህበረሰብ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የኦንላይን አገልግሎት ተግባራዊ መደረጉንም አንስተዋል።
በዚሁ ወቅት ከ90 ሺህ 644 የሚሆኑ ነጋዴዎች አዲስ የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ የተደረገ ሲሆን፤ በ2018 በጀት ዓመትም ይህንኑ ተግባራትን በማጠናከር ቁጥሩን 100 ሺህ ለማድረስ መታቀዱን ነው የገለጹት።
ፈጣን መረጃወችን ለማግኘት
https://www.facebook.com/profile.php?id=100069351701097
https://t.me/Addisababatradebureau
https://vm.tiktok.com/ZMB4AxNvr/
https://youtube.com/@addisababatradebureau-s2d...
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments