ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሚደረገው ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴን ለመቆጣጠር የሚደረገው ተግባር ተጠናክሮ ቀጥሏል
አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 24/2018(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ መቀጠሉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል እና ገበያን ለማረጋጋት ሸማቹ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝባቸው አማራጮች ተፈጥረዋል።
የገበያ ሥርዓቱ ህጋዊና ፍትሃዊ እንዲሆን የከተማዋ ንግድና ገቢዎች ቢሮ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ምክትል ሃላፊ ጸጋዬ ደበሌ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
ኢ-መደበኛ ነጋዴዎች ህጋዊ ስርዓቱን ተከትለው የንግድ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በከተማዋ ህገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች በተለይም በቅዳሜና እሁድ ገበያዎችና በገበያ ማዕከላት ውስጥ ህጋዊ መስመሩን ተከትለው እንዲሰሩ መደረጉን ተናግረዋል።
መደበኛ ያልሆኑ የንግድ እንቅስቃሴን ወደ ህጋዊ መስመር ማስገባት ፍትሃዊ የንግድ ውድድርን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ቢሮው በ2018 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህገ ወጥ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መውሰዱንና ከእነዚህም ውስጥ ከ4ሺህ በላይ የሚሆኑ ወደ ህጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ሀላፊ ሚኪያስ ሙሉጌታ በበኩላቸው፤ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ያለ ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ በተገኙ ከ2ሺህ በላይ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት።
የታክስ መሰረቱን በማስፋት ከተማዋ የምታመነጨውን ገቢ በአግባቡ ለመሰብሰብ ህግ የማስከበሩን ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ነጋዴው ግብር መክፈል ሀገራዊ ግዴታው መሆኑን አውቆ በህጋዊ መንገድ የንግድ ሥራውን እንዲከውን የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑንም ገልጸዋል።፡
ነጋዴዎች በበኩላቸው የንግድ ሥርዓቱን ፍትሃዊ ተወዳዳሪ ለማድረግ ግብራቸውን በአግባቡ በማሳወቅ በወቅቱ እየከፈሉ መሆኑን አንስተዋል።
ከነጋዴዎቹ መካከል እንዳሻው አበበ፣ ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ፍላጎቶቿን ለማሟላት ግብርን በአግባቡ መሰብሰብ አለባት ብለዋል።
የግብር ክፍያ ሥርዓቱ በዲጂታል አማራጮች የታገዘ በመሆኑ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ እርሳቸውም ግብራቸውን በወቅቱ እየተወጡ መሆኑን አመልክተዋል።
ሌላው ነጋዴ ሙስጠፋ መሃመድ ግብራቸውን በአግባቡ በመክፈል አገራዊ ግዴታቸውን እየተወጡ መሆኑን አረጋግጠዋል።
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments