ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የለሚ ሁለገ...

image description
- In ንግደረ    0

ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን መርቀው ስራ አስጀመሩ፤

ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የለሚ ሁለገብ የገበያ ማዕከልን መርቀው ስራ አስጀመሩ፤

ግንቦት 13፣ 2018 ዓ.ም.

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በለሚኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 05 ሰሚት አካባቢ የተገነባውን ለሚ ሁለገብና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል በዛሬው ዕለት መርቀው ስራ አስጀመረዋል። ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ፣ የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው ሁሉም ተግባራት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ብልጽግናዊ እሳቤን የተላበሱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩ በግብይት ስርዓቱ ውስጥ የሚፈጠረውን የገበያ ጉድለት ለመሙላትና የነዋሪዎችን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በርካታ ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ሰባት ዘመናዊና ሁለገብ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶች መሸጫ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት የከተማችን ነዋሪ ተጠቃሚ ተደርጓል ብለዋል።

በተጨማሪም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ዛሬ የተመረቀው ለሚ ሁለገብና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል የሰሚትና አካባቢው ነዋሪዎች ሁሉንም ዓይነት የሰብል ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬዎች፣ ቅመማ ቅመሞችና የፋብሪካ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ በጥራትና በብዛት በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ በማድረግ ፍትሃዊና የተረጋጋ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር እንደሚረዳ አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው፣ ለሚ ዘመናዊ ሁለገብ የገበያ ማዕከል በ2.27 ቢሊየን ብር ወጪ በ3.2 ሄክታር መሬት ላይ መገንባቱን ገልጸዋል። አክለውም ክብርት ወ/ሮ ሀቢባ፣ በከተማችን የተገነቡ ሰባቱም ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ምርቶችን በጥራትና በብዛት በማቅረብ የተረጋጋ የምርት አቅርቦትና በፍትሃዊ ውድድር ላይ የተመሰረተ ዘመናዊ የንግድ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ ቢሮው የተጣለበትን ኃላፊነት በትኩረት እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


Comments

Nothing was found.

Leave Your Comments