
በመዲናዋ የተስተዋለው የነዳጅ እጥረት በቶሎ ይቀረፋል- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ::
በመዲናዋ የተስተዋለው የነዳጅ እጥረት በቶሎ ይቀረፋል- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ
========================
አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ መጋቢት 15/2017 ዓ.ም
በዛሬው እለት በአዲስ አበባ በሚገኙ ማደያዎች የተስተዋለው ረጃጅም የተሽካርካሪዎች ሰልፍ ከአቅርቦት እጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽ እና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዮሴፍ አሰፋ ለኤኤምኤን ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ኤኤምኤን ዲጂታል በአዲስ አበባ ከተማ ተዘዋውሮ የቃኛቸው አንዳንድ ማደያዎቸ አከባቢ ረጃጅም የተሽከርካሪ ሰልፎችን አስተውላል፡፡
የተፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ የንግድ ኢንስፔክሽ እና ሬጉላቶሪ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ዮሴፍ አሰፋ ያነጋገረ ሲሆን፣ የችግሩ መንስኤ የአቅርቦት እና የዋጋ ልዩነት በመኖሩ ነው ብለዋል፡፡
ዋነኛው የችግሩ መንስኤ ግን የአቅርቦት አለመጣጣም የፈጠረው መሆኑን ያነሱት አቶ የሴፍ ቀደም ሲል በአዲስ አበባ በሚገኙ ማደያዎች በየቀኑ 3 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ባደረገው ቅኝት በዛሬው እለት ማደያዎቹ 1 ሚሊየን 292ሺ 965 ሊትር ብቻ ይዘው መገኘታቸውን ነው ያስታወቁት፡፡
በተለይም ከፍተኛ እጥረት የታየው በናፍጣ አቅርቦት መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ 39 በመቶ የሚሆኑት ማደያዎች ብቻ ናፍጣ ሲኖራቸው 61 በመቶዎቹ ናፍጣ አለማግኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ከቤንዚን ጋር ተያይዞ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑ ማደያዎች ቤንዚን ያላቸው በመሆኑ በዚህ ረገድ እጥረት የለም ነው ያሉት፡፡
ዳይሬክተር አያይዘውም፣ በማደያዎች የተስተዋለው የተሽከርካሪዎች ሰልፍ ከአቅርቦት እጥረት ጋር ተያይዞ የመጣ መሆኑን በመግለጽ፣ ችግሩ ወደብ ላይ ያለው ነዳጅ ሲገባ በቶሎ እንደሚቀረፍ ተናግረዋል፡፡
Comments
Nothing was found.
Leave Your Comments